ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013
Overview of recent political conflicts and unrest in Ethiopia, focusing on the Bench Maji Zone.
Also available in English
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 20, 2013)
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,557
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 7,713
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,203
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013)
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 26
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 398
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 37
ኢትዮጵያን በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በትጥቅ ግጭቶች ምክንያት የተፈጠረው አለመረጋጋት ባሳለፍነው ሳምንት ላይም የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች መንግስታትን መፈታተኑን ቀጥሏል፡፡ ግንቦት 14, 2013 ጠዋት ላይ የጉሙዝ ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ አባላት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 17 ታጣቂዎች የቤንሻንጉል/ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልል ወሰንን አቋርጠው ነጆ ወረዳ (ኦሮሚያ ክልል) በሚገኘው ያምበልጋራ ኦሊ ቀበሌ በግጭት ላይ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። ታጣቂ ቡድኑ ስድስት ሰዎችን ገድሏል፣ አንድ ሰው አቁስሏል፣ ቤቶችን አቃጥሏል፣ እንዲሁም ከ12 በላይ ከብቶችን ሰርቋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 16, 2013; ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 17, 2013)። የጉሙዝ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ተቀማጭነቱን ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያደረገ ሲሆን በክልሉ ውስጥ የሚሰነዘሩትን አብዛኞቹን ጥቃቶች እንደሚፈፅም ይታመናል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በመንግስት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል የሚደረገው ውጊያ ባለፈው ሳምንትም ቀጥሏል። ግንቦት 14, 2013 የኦነግ-ሸኔ አባላት ለስራ ወደ ቦሬ ቀበሌ የሚጏዙ የገላን ወረዳ ሰላም እና ደህንነት ሀይሎች ላይ አድፍጠው ጥቃት አድርሰዋል። ጥቃቱ የተከሰተው በገላን ወረዳ ጨልቤሳ ሾሮ አካባቢ ነው። በዚህ ጥቃት ምክንያት የገላን ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሀላፊ፣ የጽ/ቤቱ ባለሙያ፣ እና አምስት የፀጥታ ሃይሎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ሌሎች ስምንት ሰዎች ቆስለዋል። ስድስት የኦነግ-ሸኔ አባላት ከጥቃቱ በኋላ ከአከባቢው ሲያፈገፍጉ በኦሮሚያ የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 16, 2013)። ይህ አካባቢ የኦነግ-ሸኔ አባላት እንደሆኑ በሚታመኑ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ከሚደርስበት የአማሮ ልዩ ወረዳ ጋር ያዋሰናል (በአማሮ ልዩ ወረዳ ውስጥ በቅርቡ ስለደረሱ ጥቃቶች ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሚያዚያ 23, 2013 እስከ ሚያዚያ 29, 2013ን ይመልከቱ)።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ግብረሰናይ ድርጅቶች በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እርዳታ ለማድረስ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዳሉባቸው አስታውቋል። ይህም የሆነው አሁንም በቀጠለው ግጭት ምክንያት ነው (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ግንቦት 19, 2013)። በተጨማሪም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች ግንቦት 16, 2013 ላይ በትግራይ ክልል ሰሜን-ምዕራብ ዞን ሽሬ ከተማ ፀሃይ እና አዲ ወንፊቶ ውስጥ ከሚገኙት ተፈናቃዮች ካረፉባቸው ካምፖች ውስጥ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎችን አስረዋል። እስረኞቹ ግንቦት 19, 2013 ላይ ተለቀዋል (የኢትዮጵያ ሰባዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ግንቦት 19, 2013; ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 18, 2013; ግንቦት 20, 2013)። በእነዚህ ሶስት ቀናት ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች መደብደባቸውን ሁለት ታሳሪዎች ገልልዋል። በሶስት ቀናት የእስር ቆይታቸው እስረኞቹ የህወሃት ታጣቂዎችን እንዲለዩ ተጠይቀዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 20, 2013)።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች ወቅታዊ ሁኔታ
ጠቅላላ ምርጫው ሶስት ሳምንት እየቀሩት የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች በተለያዩ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔዎችን እየሰጡ ይገኛሉ። ግንቦት 19, 2013 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎትን ሶስት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አባላት (ባልደራስ) ለእጩነት እንዲመዘገቡ የሰጠው ውሳኔ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የአሰራር ዝርዝሮች እንዲሰጡት ጠይቋል(የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 19, 2013)። በምዝገባ ወቅት የባልደራስ ፓርቲ እነዚህን ሶስት አባላት በምዝገባ ወቅት በእጩነት ለማስመዝገብ ሲሞክር ለፍርድ ቤት ክርክር በቁጥጥር ስር ውለው እየጠበቁ ስለሆነ ምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ ፈቃደኛ አልሆነም። ከሰሞኑ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ምርጫ ቦርድ በሕጋዊና አስተዳደራዊ ውስንነቶች ምክንያት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ገልጿል። የምርጫ ወረቀቶች ታትመው ለመሰራጨት ዝግጁ መሆናቸው የመጨረሻውን ደቂቃ ለውጦች ያወሳስበዋል።
የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር ለምርጫውን መመዝገብ ካልቻሉ ሶስት አባላት አንዱ ናቸው። ግለሰቡ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውስጥ ገዥው የብልጽግና ፓርቲን የሚገዳደሩ ትልቅ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ናቸው። አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ደጋፊዎች ያላቸው በመሆኑ በመጪው ምርጫ በእጩነት ከተካተቱ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ይታመናል። መሳተፍ ከተከለከሉ የባልደራስ ፓርቲ ደጋፊዎች የሚሰጡት ምላሽ የምርጫ ብጥብጥን ሊያስነሳ ይችላል።


ቤንች ሸኮ (ወይም ቤንች ማጂ) ዞን ውስጥ ከመጀምሪያውም በክልሉ ውስጥ ነበሩ ተብለው የሚታሰቡ እንዲሁም ‘ሰፋሪዎች’ ተብለው የሚታሰቡ ሌሎች ብሄረሰቦች ይኖራሉ። ‘ሰፋሪዎቹ’ በ1970ዎቹ መጨረሻ እና ከ2007 እስከ 2008 ባለው ጊዜ ውስጥ በነበሩ የሰፈራ መርሃ ግብሮች ወደ ቤንች ሸኮ ዞን የመጡ ናቸው። በተጨማሪም ኑሮን ለማሸነፍ በንግድ እርሻዎች እና በእደ-ጥበብ የወርቅ ማዕድናት ላይ ለመስራት ወደ ክልሉ የሚጓዙ ስደተኞችም አሉ። በእነዚህ ከመጀመሪያውም በክልሉ ውስጥ ነበሩ እና ‘ሰፋሪዎች’ ተብለው በሚታሰቡ ብሄረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች ለግብአት በሚደረግ ውድድር እና የድንበር ግጭቶች ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው (ለዝርዝሩ የኢፒኦን ቤንች ሸኮ (ቤንች ማጂ) ዞን ግጭት ገፅ ይመልከቱ)። ሰኔ 2013 ላይ በቤንች ሸኮ ዞን ህዝበ-ውሳኔ ይደረጋል። ህዝበ-ውሳኔው አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ (ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፣ እና ኮንታ ልዩ ወረዳ) ደቡብ ምዕራብ ክልል የሚባል የኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ይመስርቱ ወይ የሚለውን ይወስናል። ይህ በህዝበ-ውሳኔው ካልተመረጠ አካባቢው በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አስተዳደር ስር ይቀጥላል።
ለሚዛን አማን አየር ማረፊያ የተፈቀደው ቦታ መቀየሩን ተከትሎ የቤንጭ ሸኮ ዞን ነዋሪዎች በፌዴራል መንግስት ላይ ብስጭታቸውን ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ እና የአከባቢው የመንግስት ባለስልጣናት ይህንን ውሳኔ በመቃወም ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን ይህ ውሳኔ ሌላ ግጭት ሊያቀጣጥል እንደሚችል ጠቁመዋል። አስተዳደሩ ይህ ውሳኔ “ህዝባችንን አሳንሶ ማየት” መሆኑን በአጽንኦት በመግለጽ ኃላፊነት የሚወስደው ተቋም ይቅርታ እንዲጠይቅ ጠይቋል (ቤንች ሸኮ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፣ ግንቦት 24 ቀን 2021) (የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፣ ግንቦት 16, 2013)።