- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት - 1,109
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር - 5,710
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር - 2,591
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት - 17
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር - 131
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር - 19
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በሸገር ከተማ መስጊዶችን ከማፍረስ ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ሰልፉች በአዲስ አበባ የቀጠሉ ሲሆን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ፖለቲካዊ ጥቃቶች ማለትም ጦርነቶች፣ የርቀት ጥቃቶች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል።
ባለፈው ሳምንት ግንቦት 25 ቀን ህዝበ ሙስሊሙ ከጁምዓ ሰላት በኋላ በአዲስ አበባ መርካቶ በሚገኘው ታላቁ አንዋር መስጊድ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሮቤ፣ ሻሸመኔ እና ጅማ ከተሞች እና በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ በኦሮሚያ ክልል አዲስ በተቋቋመው ሸገር ከተማ በመንግስት እየተፈጸመ ያለውን መስጊዶችን ማፈረስ በማውገዝ ሰልፎች አድርገዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ። ሰልፈኞቹ ባለፈው ሳምንት በሙስሊም ተቃዋሚዎች ላይ በመንግስት ኃይሎች የተፈጸመውን ግድያም አውግዘዋል። ግንቦት 18 ቀን የፀጥታ ኃይሎች ከጁምዓ ሰላት በኋላ በታላቁ አንዋር መስጊድ በተደረገው ሰልፍ ላይ ጥይት በመተኮሳቸው ሁለት ሰዎችን መግደላቸው እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ተቃዋሚዎችን ማቁሰላቸው ተነግሯል (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 12-18, 2015 ይመልከቱ)። ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ እና በጅማ የመንግስት ኃይሎች ሰልፈኞችን ለመበተን የኃይል እርምጃ በመውሰዳቸው ጉዳት ደርሷል። በአዲስ አበባ የመንግስት ኃይሎች – የሪፐብሊካን ጋርድ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ – የታላቁን አንዋር መስጊድ ቅጥር ግቢ ከበው በር በመዝጋት በህዝቡ ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት በመተኮሳቸው በትንሹ ሦስት ሰዎች መሞታቸው እና ያልታወቁ ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።2 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ተነጋግሮ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዲታከሙ እና ሌሎችም በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ እሳካደረገበት ምሽት ድረስ በርካታ ሙስሊም ምዕመናን ከመስጊዱ መውጣት አቅቷቸው በመስጊዱ ለመቆየት ተገደው ነበር። ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ 63 የሚጠጉ የፖሊስ አባላትም ቆስለዋል።3 በተመሳሳይ የፌዴራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት በጅማ ከተማ በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ድብደባ እና አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት መተኮሳቸው ታውቋል። በዚህም ሁለት ሰዎች ሲቆስሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል። በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ አዲስ በተቋቋመው ሸገር ከተማ እየተካሄደ ባለው የቤቶች እና መስጊዶች ፈረሳ ምክንያት ያለው ቁጣ እየጨመረ መጥቷል። እንደ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሆነ በሸገር ከተማ ከ19 ያላነሱ መስጊዶች ፈርሰዋል።4

የሸገር ከተማ ከተመሠረተ ጥር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የከተማዋ ባለስልጣናት አስፈላጊ ወረቀት የሌላቸውን ቤቶች እንዲፈርሱ ትዕዛዝ ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን ይህም የቤት ፈረሳው ኦሮሞ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ነው በሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል።5 የኦሮሚያ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊው የቤት ፈረሳውን በመደገፍ መስጊዶች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ህገወጥ ህንፃዎች እየፈረሱ መሆኑን ጠቁመው ህዝበ ሙስሊሙ “በኃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱትን የተደራጁ የውስጥ እና የውጭ ፅንፈኞችን” ችላ እንዲሉ አሳስበዋል።6 እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ያሉ ሌሎች ድርጅቶች የቤት ፈረሳ ዘመቻውን በማውገዝ አንዳንድ የፈረሱት ቤቶች የባለቤትነት ማረጋገጫ ዶክመንት አላቸው ሲሉም ተናግረዋል።7
በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ኤልያስ ወረዳ በደጎልማ ቀበሌ በሚገኘው በደብረ ኤልያስ ብሔረ በፁአን መልካ ስላሴ አንድነት ገዳም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማንነቱ ካልታወቀ ታጣቂ ቡድን ጋር ከግንቦት 18 እስከ 22 ቀን ድረስ ተዋግተዋል። መንግስት ቡድኑን የአማራ ህዝባዊ ግንባር ሲል የጠራ ሲሆን አንዳንድ እማኞች ግን እራሱን “የአለም ብርሃን” ብሎ የገለጸ ቡድን እንደሆነ ገልፀዋል።8 የተለያዩ ምንጮች ሰለደረሰው ጉዳት የሚገምቱት የተለያየ ነው። በእነዚህ ግምቶች መሰረት በግጭቱ ቢያንስ 200 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሲቆስሉ ሌሎች 10 ተገድለዋል። የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በግንቦት 25 በለቀቀው መግለጫ የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩትን እስክንድር ነጋን በዋነኛነት ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን በ“ኦፕሬሽኑ” ወቅት 200 “ታጣቂዎቹ” ተገድለዋል ብሏል።9 የደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት እንደገለጸው ቡድኑ በገዳሙ ውስጥ ስልጠና ሲሰጥ እንደነበረ እና የኃይማኖት አባቶችን፣ የአካባቢውን የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢውን ባለስልጣናት በመግደል ተሳትፏል።10
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ሁለት የእጅ ቦምቦ ጥቃቶች በክልሉ ውስጥ ተመዝግበዋል። ግንቦት 22 ቀን በደቡብ ወሎ ዞን ሳይንት ወረዳ አጅባር ከተማ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ የብልፅግና ፓርቲ አስተዳዳሪዎችን ያሳተፈ ስብሰባ እየተካሄደ ባለበት የኮንፈረንስ ማዕከል ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን የእጅ ቦምብ ወርውሯል። በኮንፈረንስ ማዕከል ላይ ጉዳት ቢደርስም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። በማግስቱ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን አምስት የአካባቢውን ሚሊሻዎች ጨምሮ ስድስት የፀጥታ ኃይሎች ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር አቁስሏል። ጥቃቱን ተከትሎ በከተማዋ የተኩስ ድምጽ ተሰምቷል። ነገር ግን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዚህ የተኩስ እሩምታ ውስጥ ማን እንደተሳተፈ የታወቀ ነገር የለም። መንግስት የክልል ልዩ ኃይል ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ የፀጥታ አካላት እንዲዋሃዱ ከወሰነ ወዲህ አማራ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ያልተረጋጋ ክልሎች አንዱ ሆኖ ቆይቷል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2015 ወርሀዊ፡ የተቀረው የአገሪቱ ክፍል ሲረጋጋ በአማራ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት ይመልከቱ)።
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ሳምንት ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በምዕራብ ሸዋ ዞን በአቡና ግንዴ በረት ወረዳ በባዳ ጢኖ እና ኤሬሪ ኬሎ ቀበሌዎች እና በሽኩቴ በጀልዱ ወረዳ እንዲሁም በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ሙዴ ላይ ተዋግተዋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ኦነግ-ሸኔ፣ ፋኖ ታጣቂ እና ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ቡድን የተፈጸሙ ቢያንስ 16 ሰዎች ህይወትን የቀጠፉ ስድስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች በክልሉ ተዘግቧል።
Footnotes
- 2
አዲስ ማለዳ፣ ‘በአንዋር መስጊድ በተከሠተ ግጭት እስከአሁን የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ፣’ ግንቦት 27, 2015
- 3
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ‘ከፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ፣’ ግንቦት 25, 2015
- 4
ሪፖርተር፣ ‘በመስጊድ በመፍረሳቸው ምክንያት ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፣’ ግንቦት 19, 2015
- 5
- 6
- 7
ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ከ111 ሺህ በላይ ቤቶች መፍረሳቸውን ኢሰመጉ አስታወቀ፣’ ግንቦት 24, 2015
- 8
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ‘ከፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ፣’ ግንቦት 25, 2015
- 9
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ‘ከፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ፣’ ግንቦት 25, 2015
- 10
የደብረ ኤልያስ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ‘ከደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት የተላለፈ መልዕክት፣’ ግንቦት 23, 2015