ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከግንቦት 21, 2013 እስከ ግንቦት 27, 2013
Current state of conflicts related to elections in Ethiopia.
Also available in English
በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 27, 2013)1
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,566
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 7,747
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,223
በቁጥር (ከግንቦት 21, 2013 እስከ ግንቦት 27, 2013)
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 3
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 3
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 1
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ካለፉት ሳምንት ጋር ሲወዳደር ባለፈው ሳምንት የነበሩት የተደራጁ ግጭቶች ኩነቶች እና ሟቾች ቁጥር አነስተኛ ነበሩ (ከዚህ በታች ያለውን ይመልከቱ)። ሳምንቱ የተጀመረው የውጭ አገራት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በሚቃወሙ ሰልፎች ነበር። ግንቦት 22, 2013 ላይ ሰልፈኞች “ድምፃችን ለነፃነታችን እና ሉአላዊነታችን” በሚል መሪ ቃል አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በማውገዝ በቅርቡ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የጣለችውን የቪዛ ገደብ እንደገና እንድታጤን ጥሪ አቅርበዋል (ፋና ብሮድካቲንግ፣ ግንቦት 22, 2013)። በአዲስ አበባ ከ50,000 በላይ ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ መካሄዱ ተዘግቧል (ኢሳት፣ ግንቦት 22, 2013)። በተመሳሳይ ቀን በአሶሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ሐረር፣ ሆሳእና፣ ስልጤ፣ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 22, 2013ሀ, የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 22, 2013ለ). በአዲስ አበባ የአሜሪካን ኤምባሲ ፊት ለፊት ሁለተኛ ሰልፍ ግንቦት 24, 2013 ላይ ተካሂዷል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ጉጂ፣ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ውስጥ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013 ይመልከቱ). ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች መካከል በሚደረገው ውጊያ መሀል የወደቁ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ኦሮምኛ ያልሆነ ቋንቋ በሚናገሩ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከባድ እርምጃ እንደተወደባቸው ቅሬታ አሰምተዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 23, 2013)።
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአጣዬና አካባቢው በፌደራል ወታደራዊ ኃይል የሚመራው ኮማንድ ፖስት የተለያዩ ተግባራትን አካሂዷል። ኮማንድ ፖስቱ የተቋቋመው በአጣዬ እና አካባቢው ባሉ አካባቢዎች ኦነግ-ሸኔ እና የአካባቢው የኦሮሞ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ሀይል እና ፌደራል ወታደሮች ጋር ከተዋጉ በኻላ ነበር (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013)። ግንቦት 25, 2013 ላይ በደሴ ከተማ ደዋ ጨፌ ወረዳ ጠረፍ ቀበሌ ባህላዊ የእርቅ ተግባራት ተካሂደዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 25, 2013)። ሆኖም ግን በአጣዬ ከተማ ውስጥ በነበረው ግጭት የተጎዱት አብዛኛዎቹ ሰዎች አብዛኛው ንብረት በግጭቱ ሙሉ በሙሉ በመውደሙ አሁንም ድረስ ግዜያዊ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 23 2013 እስከ ሚያዚያ 29 2013)።
ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂ ቡድኖች አድፍጦ ማጥቃታቸውን ቀጥለው ባለፈው ሳምንት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን የፀጥታ ኃይሎችን ገድለዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 30, 2013)። ከዚህ ጥቃት በኋላ ወደ 4000 ያህል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ከአካባቢውን ሸሽተው ሄደዋል።
ግንቦት 25, 2013 ላይ የአፋር ክልል መንግስት ላለፉት 30 ዓመታት ከትግራይ ክልል በሆኑ ሀላፊዎች ሲተዳደር የቆየውን የሳውኔ ቀበሌ አስተዳደርን እንደተረከበ ገልጿል (ዋዜማ ሬዲዮ፣ ግንቦት 25, 2013)።
Footnotes
- 1
እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- 2
ይህ ኩነት በአክሌድ በሚቀጥለው ሳምንት ይመዘገባል። በአክሌድ በአሁኑ ሰአት የመዘገበው እስከ ግንቦት 27, 2013 የተከሰቱትን የሚያሳዩ ናቸው። ይህ ኩነት የተዘገበው ግንቦት 30, 2013 ላይ ነው።