Skip to main content

ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥቅምት 20, 2014 እስከ ጥቅምት 26, 2014

Detailed weekly report on Ethiopia's political and military events.

11 November 2021

Also available in English

በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥቅምት 26, 2014)1

  • የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,150
  • በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,539
  • በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,772

በቁጥር (ከጥቅምት 20, 2014 እስከ ጥቅምት 26, 2014)2

  • የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 27
  • በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 131
  • በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 41

ኢትዮጵያን በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ

ባለፈው ሳምንት የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙትን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን መቆጣጠሩ የትህነግ ሃይሎች ወደ ደቡብ ተጉዘው ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን እና በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ ሌሎችን ቦታዎች ያስፈራሉ የሚል ስጋት በመላ ሃገሪቷ ተፈጥሮ ነበር። ይህም የፌደራል መንግስቱ ጥቅምት 23 ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አድርጓል። ቀጣዩ ክፍል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን ወቅታዊ ስጋት በዝርዝር ይቃኛል።

ሳምንቱን በሙሉ በአማራ ክልል ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ውስጥ እና አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና የአማራ ታጣቂዎች ከትህነግ ጋር መዋጋት ቀጥለዋል። ጥቅምት 25 ላይ የመንግስት ሃይሎች ጥምረት ለብዙ ወራት በትህነግ ተይዘው የነበሩትን  በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ የሚገኘውን ቆቦ ከተማ እና በትግራይ ክልል ዋጃ ከተማን መልሰው መቆጣጠራቸው ተዘግቧል።

...

መንግስት ጥቅምት 23 ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግስት ሀይሎች ግለሰቦችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲፈትሹ እና እንዲያሰሩ ይፈቅዳል። እንዲሁም የጸጥታ ስጋት ካለ መንገዶችን መዝጋት እንዲሁም የአስተዳደር መዋቅር በከፊል ወይም በሙሉ ማገድ ወይም አስተዳዳሪዎችን መተካት ይፈቅዳል (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014)። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት መሳሪያ ያለውን ወይም በቀደምት ጊዜያት ወታደራዊ አገልግሎት የሰጠን ማንኛውንም ግለሰብ ወታራዊ ስልጠና እንዲወስድ እና ወደ ወታደራዊ ተልዕኮ እንዲፈጽም አልያም መከላከያን መቀላቀል ካልቻለ መሳሪያውን እንዲያስረክብ ሊያዝ ይችላል። እስካሁን ድረስ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ሐረሪ፣ አማራ፣ እና ሶማሌ ክልሎች የሚገኙ የክልል ባለስልጣናት ተመሳሳይ ትዕዛዝ አውጥተዋል (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ጥቅምት 28, 2014አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 26, 2014)።

...

ከምርጫ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ሁኔታዎች

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መጪውን የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አጠቃላይ ምርጫ በአዲሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት አግዶታል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 26, 2014)። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በፀጥታ ችግር ምክንያት ለተዘዋወረው የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አጠቃላይ ምርጫ ጥቅምት ላይ አዲስ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ነበር። በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በሚገኙ 17 የምርጫ ክልሎች ታህሳስ 21 ለማካሄድ አቅዶ ነበር (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 9, 2014)። አሁን ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ አይታወቅም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዴ ከታወጀ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ማራዘም ይፈቀዳል።

በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ምርጫ ቦርድ ከመስከረም 2014 አጠቃላይ ምርጫ ጋር በተያያዘ በቀረቡ የምርጫ ክርክሮች ላይ ውሳኔውን አሳውቋል። ምርጫ ቦርድ ሙዬ ሙሉቄ የምርጫ ክልል (ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት) የምርጫ ካርዶች በድጋሚ እንዲቆጠሩ እና በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ በ13 የምርጫ ጣቢያዎች (ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት) አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል  (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 23, 2014)። በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሌሞ 1 እና መስቃንና ማረቆ 2 የምርጫ ክልሎች (ለተወካዮች ምክር ቤት እና ክልል ምክር ቤት) በምርጫው እለት በነበረው ማስፈራሪያ እና እንግልት ምክንያት ምርጫ ቦርድ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ወስኗል። ይህም በመስቃንና ማረቆ 2 ምርጫ ክልል ምርጫው ለሶስተኛ ግዜ ይካሄዳል ማለት ነው (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 23, 2014)።  ይሁን እንጂ እነዚህ ምርጫዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መቼ እንደሚካሄዱ አይታወቅም።

Footnotes

  1. 1

    እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።

  2. 2

    በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።

Country
Ethiopia
Share on

Related content