Skip to main content

ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥር 20-26, 2015

የኦሮሚያ ይህ ሳምንት ውጪ እና ውስጪ ግጭቶች በፕሮቶቶክሎች ዘንድ ተጨምረዋል።

9 February 2023

Also available in English

  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,253
  • በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 6,660
  • በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 2,658
  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 17
  • በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 169
  • በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 16

ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።

የኦሮሚያ ክልል በአገሪቱ ካሉ ክልሎች በጣም ያልተረጋጋ ክልል ሆኖ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ 10 የውጊያ ኩነቶች እና ስድስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል። አብዛኛው የውጊያ ኩነቶች በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች – በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ በማረሚያ ቤት ፖሊስ እና በቀበሌ ታጣቂዎች – መካከል በምስራቅ ወለጋ ዞን በአኖ ቀበሌ እና በስሬ ከተማ፣ በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ፣ በምዕራብ ጉጂ ዞን ዶጎ/ማጋዳ ቀበሌ እና ገላና ወረዳ እና በምዕራብ ሸዋ ዞን የጎዳ ገላን/ቢቲሌ ቀበሌ እና ባኮ አቅራቢያ በሚገኘው ጊቤ ወንዝ አካባቢ የተፈፀሙ ናቸው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በምስራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ስዮ ከተማ ባለፈው ሳምንት የኦነግ-ሸኔ እና የኦሮሞ ብሄር ታጣቂዎች አራት የጥበቃ ሠራተኞችን ከገደሉ በኋላ ባንኮች መዘረፋቸውም ተነግሯል።

ኦነግ-ሸኔ፣ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን እና የመንግስት ኃይሎች ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሱ ጥቃቶች ተሳትፈዋልl። ጥር 20 ቀን የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ እና በምዕራብ ሸዋ ዞን ስናን ለኩ ቀበሌ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል በትንሹ አምስት ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸው ተነግሯል። በተመሳሳይ የቀበሌ ታጣቂዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡና ግንደ በረት ወረዳ ጉዱሩ ቀበሌ የኦነግ-ሸኔ ደጋፊዎች ናቸው በማለት ሁለት ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ኦነግ-ሸኔ ባለፈው ሳምንትም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ተዘግቧል። ጥር 21 ቀን የኦነግ-ሸኔ አባላት በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ቶሬ አካባቢ በሚገኝ ደን አቅራቢያ ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ ከፍተው አንዲት ነፍሰ ጡር ሴትን ጨምሮ ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ገድለው ሌሎች አራት ሰላማዊ ሰዎችን አቁስለዋል። ተሽከርካሪው ከቡርጂ ልዩ ወረዳ ወደ ዲላ ከተማ እየተጓዘ ነበር። ከአንድ ቀን በኋላ ጥር 22 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገብረ ጉራቻ ከተማ ዘጠኝ ቻይናውያን ባረፉበት ሀበሽ ሆቴል ውስጥ የኦነግ-ሸኔ አባላት እንደሆኑ የተገመቱ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው አንድ ቻይናዊ ገድለው አንድ ኢትዮጵያዊ አግተው ወስደዋል።2 በመጨረሻም ጥር 24 ቀን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በአርሲ ዞን መርቲ ወረዳ ጎልጎታ ቀበሌ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች የገደሉ ሲሆን በንብረት ላይም ጉዳት አድርሰዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የተከሰተውን መከፋፋል ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ግጭት ተቀስቅሷል። በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ያለው አለመግባባት እየሰፋ ሲሆን መንግሥት ጣልቃ በመግባቱ ውጥረቱ እየጨመረ መጥቷል። ጥር 14 ቀን የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሊቀነ ጳጳስ አቡነ ሳዊሮስ ከሌሎች ሁለት ሊቀነ ጳጳሳት ጋር በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ በሚገኘው የሀሮ በዓለ ወልድ ቤተ-ክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ሳያውቀው 26 ጳጳሳትን ሾመው “ሁሉን ያሳተፈ ቅዱስ ሲኖዶስ” መቋቋሙን አስታውቀዋል።3 አቡነ ሳዊሮስ ምእመናን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መገልገል ባለመቻላቸው በቤተ-ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሳይፈታ የቆየውን ችግር ለመፍታት እነዚህን ሹመቶች አስፈላጊ እንደሆኑ አስረድተዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ አመራሩን በአብዛኛው “ከአንድ ቡድን” በመሾም ሁሉንም ያሳተፈ መሆን አልቻለም ሲሉ ከሰዋል።4 በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ በአቡነ ሳዊሮስ የተመራውን ሁሉንም ያሳተፈ ነው የተባለውን ሲኖዶስ ሹመት “ሕገወጥ" በማለት ሦስቱን ሊቃነ ጳጳሳት እና የተሾሙትን 25 ጳጳሳት አውግዘው ከቤተ-ክርስቲያን አግደዋል።5 ሲኖዶሱ በአቡነ ሳዊሮስ ከሚመራው ቡድን ጋር መደራደር “በተዘዋዋሪ የቤተ-ክርስቲያናችንን ህግና ስርዓት መጣሰ ነው” ብሏል።6 ሲኖዶሱ መንግሥት ቤተ-ክርስቲያንን እንዲጠብቅም ጠይቋል።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ችግሩ በውይይት ሊፈታ እንደሚገባ ተናግረዋል። በቤተ-ክርስቲያኗ በተከሰተው አለመግባባት (ችግር) መንግስት ጣልቃ እንደማይገባ አረጋግጠው ካቢኔያቸውንም ጣልቃ እንዳይገቡ ጠይቀዋል።7 ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች የኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናትን አቡነ ሳዊሮስ ለሚመራው ሁሉን ያሳተፈ ነው ለተባለው ሲኖዶስ ቡድን አንሰጥም በማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንን የደግፉ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ጳጳሳትን እና ምእመናንን ማሰር ሲጀምሩ ሁኔታው ወደ ግጭጥ ተለውጧል። እነዚህ ድርጊቶች ውዝግቡን በማባባስ ውጥረቱ እንዲጨምር ያደረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ እና አማኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና መንግስትን ህገ-መንግስቱን በመጣስ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እና ከቤተ-ክርስትያን “የታገደውን” ሌላኛውን ወገን ይደግፋሉ ሲሉ ከሰዋል።8 ጥር 27 ቀን በሻሸመኔ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ላይ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።9 ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ከጥር 29 ጀምሮ ለሶስት ቀናት የጾም፣ የጸሎት እና የእምነቱ ተከታዮች ጥቁር ልብስ እንዲለብሱ ያወጀ ሲሆን የካቲት 5 ቀን በሀገር ውስጥ እና በውጪ በሚገኙ አብያተ-ክርስቲያናትን ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል።10 የኢፒኦ ተመራማሪዎች ይህንን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተሉ ነው።

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር ተደራዳሪ ቡድን ጋር ተገናኝተዋል። በዚህ ስብሰባ በጥቅምት 2015 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አፈፃፀም የገመገሙ ሲሆን በትግራይ ክልል የቀሩትን የኤርትራ ወታደሮች፣ የባንክ አገልግሎት፣ መንገዶችን መክፈት፣ በጀት ማውጣት እና በትግራይ የሽግግር መንግስት መመስረትን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ እርምጃዎችን የሚሹ ጉዳዮችን ለይተዋል።11 ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ የሚደረጉ በረራዎች ቁጥር እንዲጨምሩ እና የባንክ ስርዓቱን አቅም ለማሳደግ ወስነዋል።12 የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት፣ ብሔራዊ ባንክ ከጥር 29 ጀምሮ 5 ቢሊዮን ብር (93 ሚሊዮን ዩኤስ ዶላር) ወደ መቀሌ መላክ የጀመረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ በሳምንት ወደ መቀሌ የሚያደርገውን በረራ ከሦስት ወደ አምስት አሳድጎል።13

Footnotes

  1. 2

    ንጋቱ ረጋሳ፣ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ራዲዮ፣ ጥር 24, 2015

  2. 3

    ኦቢኤስቲቪ፣ ‘በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ’፣ ጥር 14, 2015

  3. 4

    ኦቢኤስቲቪ፣ ‘በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ’፣ ጥር 14, 2015

  4. 5

    የኢኦተቤ ቲቪ፣ ‘አባ ጸጋዘአብ አዱኛ ይቅርታ ጠየቁ’፣ ጥር 17, 2015

  5. 6

    የኢኦተቤ ቲቪ፣ ‘የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ’፣ ጥር 18, 2015

  6. 7

    ፌስቡክ @አብይ አህመድ አሊ፣ ጥር 23, 2015

  7. 8

    የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት፣ ‘ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጡት ማብራሪያ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ’፣ ጥር 24, 2015

  8. 9

    ቪኦኤ፣ በአንድ ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ በደረሰ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ፣ ጥር 27, 2015

  9. 10

    የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የታወጀ አዋጅ፣ ጥር 27, 2015

  10. 11

    የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ‘የፌዴራል መንግሥት እና የህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ’፣ ጥር 26, 2015

  11. 12

    ዊተር @ሬድዋን ሁሴን፣ ጥር 26, 2015

  12. 13

    ቲዊተር @ሬድዋን ሁሴን፣ ጥር 27, 2015

Country
Ethiopia
Region
Africa
Share on

Related content