ኢፒኦ ሳምንታዊ: መጋቢት 30-ሚያዚያ 6, 2015
Summary of security incidents in Ethiopia for the Amhara region.
Also available in English
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,143
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 6,116
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 2,600
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 19
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 32
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 16
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ በአማራ ክልል የክልሉ ልዩ ኃይልን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅር ለመቀላቀል የታቀደውን ዕቅድ የሚቃወሙ ስልፎች የቀጠሉ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎች እነዚህን ስልፎች በኃይል መበተናቸው እና የሞት አደጋ መድረሱም ሪፖርት ተደርጓል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በክልሉ ፀጥታ ለማስከበር በተንቀሳቀሰበት ወቅትም የውጊያ ኩነቶች ተመዝግበዋል። የተቀረው የአገሪቱ ክፍል በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላማዊ ነበር።
በአማራ ክልል የክልል ልዩ ኃይልን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅር ለመቀላቀል የታቀደውን ዕቅድ በተመለከተ የሚደረገው ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በክልሉ ቢያንስ በ18 ቦታዎች የተካሄዱ ሰልፎች ተመዝግበዋል (ስለ ተነሳው ግርግር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: መጋቢት 23-29, 2015 ይመልከቱ)። በአማራ ክልል በፀጥታ ኃይሎች ቢያንስ በአምስት ቦታዎች በተወሰደው እርምጃ ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸውን አክሌድ ዘግቧል። በፌዴራል መንግስት ውሳኔ ላይ የተቀሰቀስው ቁጣ የክልሉን ልዩ ኃይል ከሌሎች የፀጥታ መዋቅር ጋር መቀላቀል የአማራ ክልል ወደፊት በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር ሊደርስበት የሚችለውን ጥቃት መከላከል እንዳይችል ያደርገዋል በሚል ፍራቻ ላይ የተመሰረተ ነው። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አምስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ውሳኔ “ህገ-ወጥ ነው” ሲሉ አውግዘዋል።2
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ውጊያዎችም ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ሚያዚያ 1 ቀን በቆቦ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የተዋጋ ሲሆን የሶስት ታጣቂዎች ህይወት መጥፋቱ ተዘግቧል። በመኪና ወደ አዲስ አበባ ይጓዙ የነበሩ ሁለት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችም በተኩሱ መሃል ተገድለዋል።3 በተጨማሪም ሚያዝያ 2 እና 3 ቀን በደብረ ብርሃን የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና አጋር የፋኖ ታጣቂዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የተዋጉ ሲሆን በከተማው አቅራቢያ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በትንሹ ሁለት ሰዎች በተባራሪ ጥይት ተመተው ህይወታቸው አልፏል።4 በሰሜን ሸዋ ዞን መዘዞ ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች እና በአማራ ክልል ፖሊስ መካከል ውጊያ የተደረገ ሲሆን ታጣቂዎቹ በከተማው የሚገኘውን ፖሊስ ጣቢያ መቆጣጠራቸውን ታውቋል።

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሠረት የክልል መንግሥታት “የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃል።”5 ሁሉም ክልሎች የፖሊስ ኃይሎች ሲኖሯቸው ልዩ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2008 የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባርን ለመመከት በሶማሌ ክልል ተቋቋመ።6 በሚያዚያ 2013 በሶማሌ እና በአፋር ክልል ድንበሮች በተከሰቱት ውጊያዎች ጨምሮ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈፀሙ ግድያዎች ላይ እጁ እንዳለበት ተመላክቷል (በሶማሌ/አፋር ክልሎች የድንበር ግጭት ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ አፋር–ሶማሌ የድንበር ግጭት ገጽን ይመልከቱ)። በሚያዚያ 2 ቀን የሶማሌ ክልል ካቢኔ የክልሉ ልዩ ኃይሎችን “እንደ ምርጫቸው በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ ውስጥ ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች” በማዋሃድ የፌዴራል መንግስትን መመሪያ ለመከተል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።7
ከ2010 ጀምሮ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ የክልል ልዩ ኃይሎች የበለጠ ተሳትፎ አድርገዋል። አክሌድ ቢያንስ 270 በልዩ ኃይሎች የተፈፀሙ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃቶችን የመዘገበ ሲሆን ይህም ከ2010 ጀምሮ የተፈጸሙ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ የጥቃት ኩነቶች 16 በመቶውን ይይዛል። ልዩ ኃይሎችን ለመበተን የተደረሰው ውሳኔ በመንግስት የሚደገፉ ግጭቶች በአጠቃላይ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል ወይም በቀላሉ ግጭቶች ወደ ሌላ የመንግስት አካል ሊዛወር ይችላል። የኦሮሚያ ክልል እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባለስልጣናት የፌዴራል መንግስትን ውሳኔ በማክበር የልዩ ኃይላቸውን በታቀደው መሠረት ወደ ሌላ የፀጥታ መዋቅር ለመቀላቀል መወሰናቸውን አስታውቀዋል።8 ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዋና ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የክልል ልዩ ኃይሎች በሀገሪቱ የፀጥታ መዋቅር ዝርዝር ውስጥ ከዚህ በኃላ እንደ ሌሉ ገልፀዋል።9
በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጉብኝት ስፖንሰር አላደረጉም በሚል ሱቆች እና ሆቴሎች መዘጋታቸውን በመቃወም የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተደርጓል።10 መጋቢት 16 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የጉራጌ ዞን እንደ ክልል እንዲቋቋም ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ለመምከር የጉራጌ ዞን አስተዳደር ማዕከል ወደ ሆነችው ወልቂጤ ከተማ ተጉዘው ነበር። ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ወቅት የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመመካከር የተመረጡት ሰዎች “ስለ ዞኑና ስለ ከተማው በቂ እውቀት የላቸውም” በማለት ከቤት ባለመውጣት ተቃውሞ አሰምተው ነበር (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: መጋቢት 16-22, 2015 ይመልከቱ)።11
Footnotes
- 2
- 3
ካቶሊክ ሪሊፍ ስርቪስ፣ ‘ካቶሊክ ሪሊፍ ስርቪስ በኢትዮጵያ ሁለት ሰራተኞችን በማጣታቸው ሀዘኑን ገለጸ፣’ ሚያዝያ 2, 2015
- 4
- 5
- 6
አዲስ ስታንደርድ፣ ‘ኒውስ አለርት፡ የሶማሌ ክልል ካቢኔ የመንግስትን የክልል ልዩ ኃይል የመበተን የመቀላቀል እቅድን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፣’ ሚያዚያ 2, 2015፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ‘ኢትዮጵያ፡ ‘ልዩ ፖሊስ’ 10 ገደለ፣’ እ.ኤ.አ ሜይ 28, 2012
- 7
- 8
ቮይስ ኦፍ አሜሪካ አማርኛ፣ ‘የኦሮሚያ ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀትን ሥምሪት ማቆሙን አስታወቀ፣’ ሚያዚያ 5, 2015
- 9
- 10
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን፣ ‘ኢሳት አማርኛ ዜና ሚያዚያ 2, 2015፣’ ሚያዚያ 2, 2015
- 11
ዮናታን ዘብዴዎስ፣ ‘ወልቂጤ ውስጥ ከቤት ያለመውጣት አድማ መደረጉን ነዋሪዎች ተናገሩ።’ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ አማርኛ፣ መጋቢት 16, 2015፤ ማኅሌት ፋሲል፣ ዩሃንስ ገብረ እግዚያብሔር፣ ‘የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጉብኝት በወልቂጤ፣’ ዶቼ ቬለ አማርኛ፣ መጋቢት 16, 2015