ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ጥቅምት 24-30, 2016
Weekly analysis of conflict-related events in Ethiopia for October 24-30, 2016.
Also available in English
- በቁጥር፡ ኢትዮጵያ, ጥቅምት 24-30, 2016
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት፡ 49
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 60
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 10
- በቁጥር፡ ኢትዮጵያ, ጥቅምት 25, 2015-ጥቅምት 30, 2016
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት፡ 1,220
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 3,800
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 1,131
ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ ኤክስፖርት መሳሪያ ማግኘት ይችላሉ።

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ተባብሰዋል። ይህ በአንዲህ እንዳለ በመንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው የሰላም ንግግር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚደረጉ ግጭቶች እንዲቀንሱ አድርጓል።
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የተባባሱ ሲሆን በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በደቡብ ወሎ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ግጭቶች ተከስተዋል(ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፋኖ ታጣቂዎችን ኢላማ በማድረግ የተፈጸመ የአየር ጥቃት በአንኮበር ወረዳ ውስጥ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት በመምታቱ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል። የፋኖ ታጣቂዎች ለአጭር ጊዜ የላሊበላ ከተማን መቆጣጠር የቻሉ ቢሆንም ጥቅምት 28 ቀን በተደረገ ውጊያ ከተማውን ለቀው ወጥተዋል። በ11ኛው ክፍለ ዘመን ከፍልፍል ድንጋይ በተሰራው እና በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በአለም ቅርስነት በተመዘገበው ቤተ-ክርስትያን አቅራቢያ የሚደረጉ ውጊያዎች እና የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች የቤተ-ክርስትያኑ ደህንነት ላይ ስጋት ፈጥረዋል።2 በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ለወራት የቀጠሉ ሲሆን እየጨመሩም ይገኛሉ።

በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ልዩ ዞን አቅራቢያ በሚገኙ አካባቢዎች በአማራ እና በኦሮሞ ብሔር ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች የተቀሰቀሱ ሲሆን ቢያንስ 18 ሰዎች ተገድለዋል። በኦሮሚያ ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን ድንበር አቅራቢያ በኦሮሞ እና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል በተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰታሉ (ተጨማሪ መረጃ የኢፒኦ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ግጭት ገጽን ይመልከቱ)።
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (በመንግስት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው) እና በፌዴራል መንግስት ተወካዮች መካከል ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር በታንዛንያ እየተካሄደ መሆኑን ምንጮች ጥቅምት 27 ቀን ይፋ አድርገዋል። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ድሪባን እና በኃላ ላይ ንግግሩን የተቀላቀሉት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደኀንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን እና የኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስተር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቴዎስን ጨምሮ ከሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።3 ከዚህ በፊት የተደረገው የመጀመሪያ ዙር የሰላም ንግግር በሚያዝያ 2015 ያለ ስምምነት ተጠናቋል (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2015 ወርሀዊ፡ የሰላም ንግግር ቢሞከርም በኦሮሚያ ዳግም ግጭት ተቀስቅሷል ይመልከቱ)። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፓርቲ እ.ኤ.አ 2019 ከተገነጠለ ጊዜ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔን ያሳተፈ ውጊያ የቀጠለ ሲሆን በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ 1.4 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ተፈናቅሏል።4
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ግጭት ቀጥሏል። ጥቅምት 30 ቀን ማንነታቸው ያልታወቀ ወጣቶች የአበሩስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም 30 ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ድርጊቱ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ጣልቃ በመግባቱ ሊቆም ችሏል። በጉራጌ ዞን በተለይም በወልቂጤ ከተማ ያለው ግጭት ከጥቅምት ጀምሮ እንደቀጠለ ነው። በቅርቡ የተመሠረተው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞንን ለሦስት የአስተዳደር መዋቅሮች የከፈለ ሲሆን የምስራቅ ጉራጌ ወረዳን ዞን ሆኖ እንዲደራጅ ሲወስን የቀቤና እና የማረቆ ወረዳዎች እያንዳንዳቸው ‘ልዩ’ ወረዳ ሆነው እንዲዋቀሩ ተደርጓል።5 ከዚህ ውሳኔ ጊዜ ጀምሮ ከዚህ በፊት በወሰን ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት በተደጋጋሚ ገጭቶች በሚከሰቱባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
በትግራይ ክልል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በትግራይ ሕዝብ ነጸነት ግንባር (ትሕነግ/ሕወሓት) መካከል ከተፈጠረው ውዝግብ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት ሁለት የዞን አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ አራት ተጨማሪ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል።6 አራቱም ባለስልጣናት የትሕነግ/ሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሲሆኑ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።7 ይህ ውሳኔ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሌሎች ስድስት አስተዳዳሪዎች ከስልጣን የተባረሩበትን እርምጃ ተከትሎ የመጣ ነው (ለተጨማሪ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ፡10-16 ጥቅምት 2016ን ይመልከቱ)።
Footnotes
- 2
አልጀዚራ፣ ‘የኢትዮጵያ ወታደሮች የኦርቶዶክስ ቅድስት ቦታ ከሆነችው ከላሊበላ ከተማ ታጣቂ ቡድንን አስወጡ፣’ ጥቅምት 29, 2016
- 3
- 4
- 5
ዋዜማ ራዲዮ፣ ‘የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕልውና በይፋ አከተመ፣’ ነሐሴ 13, 2015
- 6
አዲስ እስታንዳርድ፣ ‘የፖለቲካ ዜና፡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተጨማሪ አራት ከፍተኛ ባለስልጣናትን አባረረ፣’ ጥቅምት 28, 2016
- 7
ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘በትግራይ አራት አመራሮች ከሓላፊነት የተነሡት “ሥራን ለመፈጸም ባለመቻል” እንደኾነ ክልሉ ገለጸ፣’ ጥቅምት 28, 2016