Skip to main content

ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ኅዳር 15-21, 2016

Recent political conflicts in Oromia and Amhara claim many lives, with continuing clashes and military actions.

8 December 2023

Also available in English

በቁጥር፡ ኢትዮጵያ, ኅዳር 15-21, 20161

  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት፡ 31
  • በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 137
  • በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 59

  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,256
  • በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 3,859
  • በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 1,357

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የፖለቲካ ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን የብዙ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ ክስተቶች ተዘግበዋል። በአንጻሩ ሌሎች የሀገሪቷ አካባቢዎች ሰላማዊ ሆነው ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ በሚጠራው) መካከል በታንዛንያ የተደረገው የሰላም ንግግር ኅዳር 11 ቀን ያለስኬት ከመጠናቀቁ በፊት እና በኋላ ባሉት ቀናት በኦሮሚያ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛ ጭማሪ አሳይተዋል። ኅዳር 22 ቀን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔን “የመዋጋት ጥረቱን ማጠናከሩን” ገልጿል።2 ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔ መካከል በምስራቅ ወለጋ ዞን ኢበንቱ ወረዳ በተደረጉ ውጊያዎች በግምት 11 የሚሆኑ የሟቾች ቁጥር ተዘግበዋል። 

በኅዳር 14 እና 17 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ማንነታቸው በውል ያልተለዩ ታጣቂዎች በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ለሙ እና ሶሌ ዲገሉ ቀበሌዎች ቢያንስ 36 ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል።3 የጥቃቱ ሰለባ በዋነኝነት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሲሆኑ በብሔር አማራ ናቸው። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለጥቃቱ ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔን የከሰሰ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔ ቃል አቀባይ በበኩሉ ውንጀላውን አስተባብሎታል።4 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ባወጣችው መግለጫ ግድያውን አውግዛ ጥቃቱን በማስመልከት “የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዝምታ” ላይ ቅሬታ አሰምታለች።”5 ጉባኤው ለሁሉም የኃይማኖት ተቋማት ድምጽ ለመሆን እና የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመ ነው። በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ዘጠኝ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ አባላት ባልታወቁ ታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸው ከተዘገበ ከሦስት ቀን በኋላ አስክሬናቸው ተገኝቷል። አንዳንድ ምንጮች ለጊዳሚ ወረዳ ግድያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ተጠያቂ አድርገው ዘግበዋል።6 ይህ በእንዲህ እንዳለ የወንጌላዊያን ቤተ-ክርስቲያን ለግድያው ማንነቱ ያልተገለፀ ቡድንን ተጠያቂ በማድረው መንግሥት የድርጊቱን ፈፃሚዎች ለፍትህ እንዲያቀርብ ጠይቃለች7 (በኢትዮጵያ ኃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ወርሃዊ፡ ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014ን ይመልከቱ)።

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች እንደቀጠሉ ሲሆን በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ወሎ እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ጦርነቶች መደረጋቸው ተዘግቧል (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የተቆጣጠሩት ቦታ መኖሩ ባይዘገብም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን በጢስ አባይ እና በባሕር ዳር ከተሞች መካከል ባለው ዋና መንገድ ላይ በሚገኘው የነገደ ማርያም አካባቢ ተዋግተዋል። ይህ ጦርነት የመከላከያ ሠራዊት በፋኖ ታጣቂዎች ስር የምትገኝ መሆኑ የሚነገረው የጢስ አባይ ከተማን ለመቆጣጠር ከመሞከሩ ጋር በተያያዘ ነው።8

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ሚያዝያ 2015 በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከርቀት የሚፈፀሙ ጥቃቶች ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው። ባለፈው ሳምንት ብዙ የሰው አልባ አውሮፕላን እና የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች መፈፀማቸው የተዘገበ ሲሆን እነዚህ ጥቃቶች በአማራ ክልል ከተዘገቡ ግድያዎች 72% ይሸፍናሉ። ኅዳር 17 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በፋኖ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ በፈፀመው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በምስራቅ ጎጃም ቡቢኝ ወረዳ ዋበር የሚገኝ ምግብ ቤትን የመታ ሲሆን ቢያንስ 20 ሰዎች ተገድለዋል። ከሁለት ቀን በኋላ ኅዳር 19 ቀን በሰሜን ወሎ ዞን ቡጊና ወረዳ በሲኖ ትራክ መኪና በመጓዝ ላይ የነበሩ የፋኖ ኃይሎች ላይ በማነጣጠር በተፈፀመ ሌላ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በአንዳንድ ምንጮች ግምት መሠረት ብዛታቸው እስከ 50 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።9 ነግር ግን የተጠቀሰውን የሟቾች ቁጥር ማረጋገጥ አልተቻለም። ኅዳር 20 ቀን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኃይሎች የተተኮሰ ከባድ መሳሪያ በደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማ ከደላንታ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል ውጪ ላይ የሆስፒታሉን አምቡላንስ የመታ ሲሆን ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገድለዋል። በመጨረሻም ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕርዳር ሁለት የእጅ ቦምብ ጥቃቶች መፈፀማቸው የተመዘገበ ሲሆን በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት ግን የደረሰ ምንም ጉዳት የለም።

ከኦሮሚያ እና አማራ ክልል ውጪ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ግጭቶች እየቀነሱ ሲሆን ይህ ደግሞ የፖለቲካ ግጭቶች በተመሳሳይ ወቅት በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይከሰቱ ከነበረበት ከባለፉት ዓመታት ጋር እጅግ የሚቃረን ነው። ጉልህ የግጭት መቀነስ ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን፣ የጋምቤላ ክልል እና በቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካባቢዎች የወላይታ ዞን እና የአሌ ልዩ ወረዳን ጨምሮ ያሉ አካባቢዎች ይገኙበታል።

Footnotes

  1. 1

    በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ.

  2. 2

    አዲስ ስታንዳርድ፣  ‘የኦሮሚያ ክልል መንግስት በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገለፀ፣’ ኅዳር 22, 2016

  3. 3

    ሮይተርስ፣ ‘የኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል የኦነሠ አማፂዎችን “ብዙ” ሰዎችን ገድሏል በማለት ከሰሰ፣’ ኅዳር 22 ,2016

  4. 4

    አዲስ ስታንዳርድ፣  ‘ዜና: በኦሮሚያ ክልል በአርሲ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች በተፈፀሙ ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች 45 አማኞች ተገደሉ፣’ ኅዳር 21, 2016

  5. 5

    ዲደብሊው አማርኛ፣ ‘የማክሰኞ ኅዳር 25, 2016 የአለም ዜና፣’ ኅዳር 25, 2016

  6. 6

    አዲስ ስታንዳርድ፣  ‘ዜና: በኦሮሚያ ክልል በአርሲ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች በተፈፀሙ ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች 45 አማኞች ተገደሉ፣’ ኅዳር 21, 2016

  7. 7

    የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ ‘በቄሌም ወለጋ ዞን፤ በጊዳሚ ወረዳ በአባላቶቿ ላይ የደረሰውን ግድያ አስመልከቶ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የተሰጠ መግለጫ፣’ ኅዳር 25, 2016

  8. 8

    የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ ‘በቄሌም ወለጋ ዞን፤ በጊዳሚ ወረዳ በአባላቶቿ ላይ የደረሰውን ግድያ አስመልከቶ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የተሰጠ መግለጫ፣’ ኅዳር 25, 2016

  9. 9

    የኢትዮጵያ የሚዲያ አግልግሎት፣ ‘ኢኤምኤስ ዜና ሐሙስ ኅዳር 20, 2016፣’ ኅዳር 20, 2016

Country
Ethiopia
Region
Africa
Share on

Related content