Skip to main content

ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ኅዳር 8-14, 2016

Weekly analysis of conflicts in Ethiopia focusing on political tensions and peace negotiations.

1 December 2023

Also available in English

በቁጥር፡ ኢትዮጵያ, ኅዳር 8-14, 2016

  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት፡ 34
  • በፖለቲካ ግጭቶች ምክኒያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 89
  • በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክኒያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 18

በቁጥር፡ ኢትዮጵያ, ኅዳር 9, 2015 -ኅዳር 14, 2016 

  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት፡ 1,236
  • በፖለቲካ ግጭቶች ምክኒያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 3,792
  • በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር፡ 1,309

ኢትዮጵያን የሚመለከቱ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ። 

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ

ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የሰላም ንግግር መክሸፉን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ግጭቶች የጨመሩ ሲሆን በአማራ ክልልም ውጊያዎች ቀጥለዋል።

በፌዴራል መንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (በመንግስት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው) መካከል ሲካሄድ የነበረው የሰላም ንግግር ከስምምነት ሳይደርሱ ኅዳር 11 ቀን ተጠናቋል። መንግስት የሰላም ንግግሩን አለመሳካት ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔ አመራር “ለሰጥቶ መቀበል ዝግጁ አለመሆን” ጋር አያይዟል።2 በምላሹ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔ አመራር “የቀረበለትን ሰልጣን” አለመቀበሉን እና የመንግስት ተወካዮች “ለአገሪቱ መሠረታዊ የፖለቲካ እና የደህንነት ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት አላሳዩም” በማለት ወቅሷል።3 ይህ በሁለቱ ወገኖች መካከል ከጥቅምት የመጨረሻ ሳምንታት ጀምሮ በታንዛንያ ዳረ ሰላም የተካሄደ የሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር ነው። ከሚያዝያ 19-25, 2015 የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የሰላም ንግግር በተመሳሳይ ከስምምነት ሳይደረስ ተጠናቋል። የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታን ጨምሮ አንጋፋ ፖለቲከኞች፣ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና ማህበረሰቡ የሰላም ንግግሩ ያለስኬት በመጠናቀቁ ቅር መሰኘታቸውን የገለፁ ሲሆን አንዳንዶቹ የሰላም ንግግሩ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት በመንግስት የተወሰዱ ወታደራዊ አርምጃዎችን አውግዘዋል።4

የሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር በጀመረበት ሳምንት ማለትም ከጥቅምት 24-30 ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔ የተሳተፈባቸው የፖለቲካ ግጭቶች ከዚያ በፊት ከነበሩ ሳምንታት ጋር ሲነፃፀር በ80% ቀንሰው ነበር። ሆኖም ግን የሰላም ንግግሩ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ በክልሉ ግጭቶች መጨመር የጀመሩ ሲሆን ከኀዳር 1 ቀን ጀምሮ ውጊያዎች አንደገና ጀምረዋል። ባለፈው ሳምንት በክልሉ ከሚገኙ 20 ዞኖች መካካል በ11ዱ ውስጥ 19 ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በዚህም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦነግ-ሸኔ መካከል በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በቡኖ በደሌ፣ በቦረና እና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። ኅዳር 13 ቀን በቡኖ በደሌ ዞን መንግስት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት/ኦነግ-ሸኔ ኃይሎችን ኢላማ በማድረግ የአየር ጥቃት የፈፀመ መሆኑን የተነገረ ሲሆን ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች አና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች እንደ ቀጠሉ ሲሆን በምስራቅ ጎጃም እና በሰሜን ወሎ ዞኖች ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። የፋኖ ታጣቂዎች ኅዳር 13 ቀን ከመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመዋጋት በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ የሚገኘውን የማረሚያ ቤት ተቆጣጥረዋል። የፋኖ ታጣቂዎች የታጣቂ ቡድኑ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 600 ታራሚዎችን ካስለቀቁ በኃላ ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል። ምንም እንኳን አብዛኛውን የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ቢሆኑም በወልዲያ የተፈፀመው አይነት መጠነ ሰፊ ጥቃት በአብዛኛው የተበታተኑ የፋኖ ታጣቂዎች አቅማቸው እየጨመረ ስለመምጣቱ ሊያሳይ ይችላል ((በአማራ ክልል ስላለው ግጭት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ወርሃዊ: ከሐምሌ 25 አስከ ነሐሴ 25, 2015ን ይመልከቱ)።

በመጨረሻም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ሰዎች በተማሪዎች ላይ በፈፀሙት ጥቃት አንድ ሰው ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ገብቷል። በምስክሮች መሠረት ጥቃቱ ማንነትን መሠረት ያደረገ ነው።5 ይህ ጥቃት ከጥቅምት 21 እስከ ኅዳር 20, 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በተማሪዎች ላይ የተፈፀመ ሁለተኛው ጥቃት ነው (ለተጨማሪ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ጥቅምት 24-30, 2016ን ይመልከቱ)። በወልቂጤ ከተማ እና በአቅራቢያው በሚገኘው የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር እና በአስተዳደሩ ውስጥ ሊኖር ከሚገባው የብሔሮች ውክልና ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ግጭቶች እየተከሰቱ ሲሆን ከተማዋ በአሁኑ ጊዜ በፌዴራል ኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ስር ትገኛለች (ለተጨማሪ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ መስከረም 26-ጥቅምት 2, 2015ን ይመልከቱ)።

Country
Ethiopia
Region
Africa
Share on

Related content