Skip to main content

ኢፒኦ ሳምንታዊ ዘገባ (ግንቦት 13, 2016)

የአማራ ክልል ፋኖ ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት የሰላማዊ ሞትን አስከትሏል።

24 May 2024

Also available in English

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ

በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት የሰላማዊ ሰዎችን ሞት አስከትሏል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እና በጋምቤላ ክልል እንደገና ግጭት ተቀስቅሷል።

በአማራ ክልል ውስጥ በተፈፀሙ የአየር ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ተመቱ

በአማራ ክልል በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በደቡብ ወሎ እና በሰሜን ወሎ ዞኖች ውጊያዎች  መደረጋቸው ተዘግቧል። ከውጊያዎቹ በተጨማሪ መንግሥት ግንቦት 4 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ውስጥ የሰባት ሰላማዊ ሰዎች ህይወትን እንደቀጠፈ የተነገረለትን ጥቃት ጨምሮ ብዙ የአየር ጥቃቶችን ፈጽሟል። በተመሳሳይ ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ በተፈፀመ ሁለተኛ የአየር ጥቃት ሦስት የፋኖ አባላት እና አራት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በመንግሥት የሚደረገው የአየር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ የነበረ ሲሆን አሁንም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የመንግሥት የፀረ አማፂያን ስትራቴጂ ዋና አካል ሆኖ ቀጥሏል። በተዋጊ አውሮፕላኖችም ሆነ በሰው አልባ አውሮፕላኖች  የሚፈፀሙ የአየር ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተላቸው ቅሬታ ፈጥረዋል። የካቲት 2016 በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃን ወደራ ወረዳ በተሽከርካሪ ላይ በመንግሥት የተፈፀመ የአየር ጥቃት 30 ሰዎችን በመግደል ሌሎች 15 ሰዎችን ማቁሰሉ ሪፖርት ተደርጓል። በአማራ ክልል ከነሐሴ 2015 ጀምሮ በተፈፀሙ 29 የአየር ጥቃት ክስተቶች ቢያንስ 323 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ውጊያዎች 

ግንቦት 6 ቀን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የተነሱ ታጣቂዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ/አማሮ ዞን ከመጡ ማንነታቸው ካልተገለፀ ታጣቂዎች ጋር ለሁለት ቀናት የተዋጉ ሲሆን በዚህም ውጊያ ሦስት ሰዎች መገደላቸው 1ተነግሯል። የአካባቢው የመንግሥት አካላት ውጊያው መደረጉን አረጋግጠው ውጊያውን ለማስቆም ከፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ጠይቀዋል።

የምዕራብ ጉጂ እና አማሮ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ሲሆን የሁለቱ ዞኖች የአስተዳደራዊ ወሰን  የይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዙ ናቸው።

በጋምቤላ እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ችግር

በጋምቤላ ክልል ለሁለተኛ ሳምንት ግጭት ቀጥሏል። ግንቦት 4 እና 5 በኢታንግ ልዩ ወረዳ ፉልኮርሴ በተባለ ቀበሌ የክልሉ ፖሊስ ማንነቱ ካልተገለፀ ታጣቂ ቡድን ጋር ተዋግቷል። በውጊያው ቢያንስ ስድስት ሰላማዊ ሰዎች እና ሶሰት የፀጥታ ኃይል አባላት የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎች ቆስለዋል። ታጣቂዎቹ ቤቶችን ያቃጠሉ ሲሆን ይህን ግጭት ተከትሎ ቢያንስ 10370 ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።2 ውጊያውን ተከትሎ የጋምቤላ ከተማን ከኢታንግ ልዩ ወረዳ ጋር የሚያገናኘው መንገድ ለጊዜው ተዘግቶ ነበር። ውጊያው የተጀመረው የፀጥታ ኃይሎች ማንነቱ ያልተገለፀ ታጣቂ ቡድንን ትጥቅ ለማስፈታት ሙከራ ማድረጋቸውን ተከተሎ ነው።3 

ጋምቤላ ክልል ለዓመታት ሰላማዊ ሆኖ የሰነበተ ቢሆንም ከግንቦት 2015 ጀምሮ በኢታንግ ልዩ ወረዳ እየተከሰተ ያለው አለመረጋጋት የክልሉን ሰላም በመቀልበስ በክልሉ ግጭት እየጨመረ ይገኛል። ሚያዝያ 11 ቀን የክልሉ መንግሥት በክልሉ እየጨመረ ከመጣው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሥራ የተባረሩ የሥራ ኃላፊዎችን ለመተካት ለስምንት አዳዲስ ኃላፊዎች ሹመት ሰጥቷል።4

ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ግንቦት 3-9, 2016

ይህ መረጃ/ዳታ ከግንቦት 3 እስከ 9, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።

  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች: 385
  • +31% ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር
  • የሰልፍ ኩነቶች: 26
  • 0% ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር (ባለፈው ሳምንት 0 የሰልፍ ኩነት ነበር)
  • ውጊያዎች: 13 ኩነቶች
  • ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 5 ኩነቶች
  • ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 20 ኩነቶች
  • የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
  • ሰልፎች: 2 ኩነቶች
  • ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት

Footnotes

  1. 1

    ዮናታን ዘብዴዎስ፣ ‘በደቡብ ኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዳግም በተነሣ ግጭት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 7, 2016

  2. 2

    ገ/ሚካኤል ገ/መድህን፣ ‘በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተከሰተ ግጭት 11 ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ፣’ ቪኦኤ አማርኛ, ግንቦት 7, 2016

  3. 3

    ነጋሳ ደሳለኝ፣ ነጋሽ መሐመድ እና ታምራት ዲንሳ ‘በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት አለፈ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 6, 2016

  4. 4

    የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ፣ ‘የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለስምንት አዳዲስ የሥራ ኃላፊዎች ሹመት ሰጠ፣’ ሚያዝያ 11, 2016

  5. 5

    ይህ ውጊያዎችን፣ ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚመለከቱ ኩነቶችን እንዲሁም የአመፅ ግጭት ንዑስ ኩነት የሆነውን የአመፅ ኩነትን ይጨምራል።

  6. 6

    ይህ የተቃውሞ ሰልፎች የኩነት አይነትን እንዲሁም የአመፅ ግጭት ንዑስ ኩነት የሆነውን ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ ኩነትን ይጨምራል።

Related content