ኢፒኦ ሳምንታዊ ዘገባ (ጥር 21, 2016)
ጥቅምት ወር ወቅት በኢትዮጵያ ኤንዲክቤት ሃይሎቻቆትና የአማራ ብሔራዊ ትብበሩባ ከሜዴር አንኳኳቃትሪቡት
Also available in English
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ብዙ ቦታዎች በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች የተዘገቡ ሲሆን በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚካሄደው ጦርነት ቀጥሏል። በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (አነግ)-ሸኔ ተብሎ በሚጠራው — መካከል ጠንከር ያሉ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የባለፈው ሳምንት ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር የግጭት መጠን ቀንሷል።
የተቃውሞ ሰልፎች በትግራይ ክልል
ጥር 13 ቀን በትግራይ ክልል የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መቐለ፣ አዲግራት፣ አድዋ፣ ሽሬ፣ አክሱም፣ ሽራሮ፣ ቆላ ተምቤን፣ ጉሎ መቀዳ እና ኢሮብን ጨምሮ በአጠቃላይ በስምንት ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ወደ “ቀዬያቸው እንዲመለሱ” እና ምግብ እና መድኃኒት አለመኖሩ በመግለፅ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ድምጻቸውን አሰምተዋል።1 በተጨማሪም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ በተለየ መልኩ አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት “የፀጥታ ሁኔታው ሲፈቅድ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች የሚመለሱበት እና ከማኅበረሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል” የሚል አንቀጽ ይዟል።2 የተቃውሞ ሰልፈኞቹ እንደገለጹት በጥቅምት 2015 ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በትግራይ ክልል እጅግ ውስን ግጭቶች ብቻ ተመዝግበዋል። ይሁንና አንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በተጨባጭ በአማራ ክልል አስተዳደር ቁጥጥር ስር የሚገኙ በመሆናቸው ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው መመለስ አልቻሉም። የአማራ ክልል በአሁኑ ጊዜ የምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ዞኖች አካባቢዎችን ይቆጣጠራል። ስምምነቱ ከተፈረመ ከአንድ ዓመት በኋላ የፌዴራል መንግሥት “የይገባኛል ጥያቄ ከተነሳባቸው አካባቢዎች” የመጡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱ መሆኑን እና የአካባቢዎቹ ቀጣይ እጣ ፋንታ በሕዝበ ውሳኔ የሚወሰን መሆኑን አስታውቋል።3 በአሁን ጊዜ ከመንግሥት ጋር በጦርነት ላይ የሚገኙት የፋኖ ታጣቂዎች እና ብዙ የአማራ ብሔር ተወላጆች በምዕራብ ትግራይ ዞን ውስጥ የሚገኙት የወልቃይት፣ ሁመራ እና ፀለምት አካባቢዎች እና በደቡብ ትግራይ ዞን ውስጥ የሚገኘው ራያ የአማራ ክልል ግዛት መሆኑን በመጥቀስ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳሉ። በአማራ ክልል ባለው የደህንነት ችግር እና የኢትየጵያ መከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ ምክንያት የእነዚህን አካባቢዎች እጣ ፋንታ ለመወሰን ማንኛውንም ሕዝበ ውሳኔ በቅርቡ ለማድረግ ያለው እድል እጅግ ያነሰ ነው (የይገባኛል ጥያቄ በተነሳባቸው የምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ዞኖች አካባቢዎችን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ትግራይ ክልል ገፅ እና ኢፒኦ ሳምንታዊ ፡ ሐምሌ 22-28, 2015ን ይመልከቱ)።
በአማራ ክልል የተደረጉ ውጊያዎች
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ውጊያዎች ተመዝግበዋል። አብዛኛዎቹ የውጊያ ኩነቶች በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የተከሰቱ ናቸው። ይሁንና ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር ባለፈው ሳምንት በክልሉ የተከሰቱ ውጊያዎች በ60% ቀንሰዋል። ባለፉት ሁለት ወራት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ሁለት ጊዜ ከአማራ ክልል አመራሮች ጋር በመገናኘት በክልሉ መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሰላም ንግግር ለማድረግ ያሉ እድሎች ላይ ተወያይተዋል።4 ሁሉን አቀፍ እና አካታች የሰላም ንግግር ለማድረግ ያልተማከለ የፋኖ አደረጃጋት ዋንኛ መሰናክል ሆኗል። በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ነሐሴ 2015 የጀመረ ነው (ለተጨማሪ መረጃ የኢፒኦ ወርሃዊ፡ ታኅሣሥ 2016፣ የኢፒኦ ወርሃዊ፡ ነሐሴ 2015 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ሐምሌ 22-28, 2015ን ይመልከቱ)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዋግ ኽምራ ዞን የአማራ ክልላዊ መንግሥት ቀደም ሲል በአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዲን) ስር በነበሩ በአበርገሌ ወረዳ ስር ወደ ሚገኙ 12 ቀበሌዎች የመንግሥት ሠራተኞችን ማሰማራት ጀምሯል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግጭት ወቅት አዲን ከትህነግ/ህወሓት ጎን በመሰለፍ የተዋጋ ሲሆን በዞኑ ውስጥ የሚገኙ 17 ቀበሌዎችን — 12 ቀበሌዎች በአበርገሌ ወረዳ እና አምስት ቀበሌዎች በጻግብጂ ወረዳ — ተቆጣጥሯል። ታኀሣሥ 13 ቀን አዲን እና የአማራ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ስምምነት የፈረሙ ሲሆን በስምምነቱ መሠረት የአዲን ታጣቂዎች መሳሪያቸውን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲያስረክቡ እና ንቅናቄው በፖለቲካ ፓርቲነት እንደሚመዘገብ ተቀምጧል። ይሁንና በአዲን አመራሮች መሠረት ትጥቅ የመፍታት ሂደቱ እስኪከናወን ድረስ የአዲን ኃይሎች የቀበሌዎቹን የፖለቲካ እና የፀጥታ ጉዳዮችን ማስተዳደራቸውን ይቀጥላሉ።5
በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት
በኦሮሚያ ክልል በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን በመንግሥት የሚፈፀሙ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶችም ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየጨመሩ ይገኛሉ። ምንም እንኳን በሰሜን ሸዋ ዞን ውጊያዎች መደረጋቸው የተዘገበ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት አብዛኛዎቹ ውጊያዎች የተደጉት በክልሉ ደቡባዊ ክፍል ነው። ጥር 12 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳና ማሊማ ወረዳ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ይዞታዎችን ኢላማ በማድረግ ሦሰት የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶችን ፈጽሟል። በቀጣዮ ቀን በምስራቅ ጉጂ ዞን አዶላ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ሁለት ተጨማሪ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶች መፈፀማቸው እና በጥቃቱም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶቹ እንዳሉ ሆነው ጥር 13 እና 14 በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ ጠንካራ ውጊያ መደረጉ ተዘግቧል። ጥር 14 ቀን የሪፐብሊካን ጋርድ ኃይሎች6 የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ኃይሎችን ኢላማ በማድረግ በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ዘመቻ አካሂደዋል። ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር — ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ በሚያዝያ 2011 የተገነጠለበት የፖለቲካ ፓርቲ — በኦሮሚያ ክልል እየተካሄዱ ያሉ የአየር ጥቃቶችን በማውገዝ መንግሥትን “በአረመኔያዊነት እና በግዴለሸነት” ከሷል።7
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥር 14 ቀን የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምዕራብ ጉጂ ዞን በቀበሌ ታጣቂዎች ላይ የደፈጣ ጥቃት በመፈፀም 12 ታጣቂዎችን ገድለው ሁለት አቁስለዋል። ጥቃቱ በአካባቢው የነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ከአካባቢው ለቀው ከወጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተፈፀመ ነው።
የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የተገኙበት ሁለት ዙር የሰላም ንግግር ሙከራዎች ቢደረጉም በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት ለዓመታት ሳይገታ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት የተደረገውን የብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሸመልስ አብዲሳ ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ጋር “መንግሥት የሰላም ንግግሩን ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን” ጠቁመዋል።8

ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ጥር 11-17, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከጥር 11 እስከ 17, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
Footnotes
- 1
ሙሉጌታ አጽብሃ፣ ‘ምላሽ ያላገኙ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ድጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ አካሔዱ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 13, 2016
- 2
- 3
- 4
ዋዜማ፣ ‘የኦሮምያና የአማራ ክልል አማፅያንን ከመንግሥት ጋር ለማደራደር አዲስ ሙከራዎች እየተደረጉ ነው፣’ ጥር 14, 2016
- 5
ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በአገው ታጣቂዎች ወደተያዙ የዋግ ኽምራ ቀበሌዎች የመንግሥት ሠራተኞችን ማስገባት ተጀመረ፣’ ጥር 13, 2016
- 6
ዳንኤል መምበረ፣ ‘ፎቶ፡ ‘ሪፐብሊካን ጋርድ’ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጠበቅ ዝግጁነቱን አሳየ፣’ አፍሪካ ኒውስ፣ ታኅሣሥ 14, 2011
- 7
- 8
አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር የተቋረጠውን የሰላም ንግግር ለመቀጠል ዝግጁነት መኖሩን ጠቆሙ፣’ ጥር 18, 2016
- 9
ይህ ውጊያዎችን፣ ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚመለከቱ ኩነቶችን እንዲሁም የአመፅ ግጭት ንዑስ ኩነት የሆነውን የአመፅ ኩነትን ይጨምራል።
- 10
ይህ የተቃውሞ ሰልፎች የኩነት አይነትን እንዲሁም የአመፅ ግጭት ንዑስ ኩነት የሆነውን ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ ኩነትን ይጨምራል።