የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በፈረንጆቹ አዲሱ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የፖለቲካ ግጭት ማስተናገዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን ሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎች በአንጻራዊነት የተረጋጉ ሆነው ሰንብተዋል። በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የአየር ጥቃቶችን ጨምሮ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (አነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በፀጥታ ኃይሎች እና ማንነቱ በውል ባልተገለጸ ታጣቂ ቡድን መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል ያለው አለመረጋጋት
በኦሮሚያ ክልል በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች መካከል የሚደረግ ጦርነት የቀጠለ ሲሆን በሁለቱ ኃይሎች መካከል በጉጂ እና በምዕራበ ሸዋ ዞኖች ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ተወካዮች ታኅሣሥ 23 ቀን የትራንስፖርት አድማ ማወጃቸው የተነገረ ሲሆን ይኸውም ታኅሣሥ 28 ቀን በተከበረው የኢትዮጵያ የገና በዓል ወቅት መንገዶች እንዲዘጉ እና መጓጓዣ ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል።1 ታኅሣሥ 29 ቀን የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ አባላት መሆናቸው የተጠረጠሩ ኃይሎች በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ ከተማ አቅራቢያ ሦስት ሾፌሮችን ተኩሰው በመግደል መኪኖቻቸውን አቃጥለዋል። ተጎጂዎቹ በታጣቂዎቹ የታወጀውን የትራንስፖርት አድማ በመጣስ በጥቃት አድራሽ ታጣቂዎች ተከሰዋል።2
ውጊያ በአማራ ክልል
በአማራ ክልል ከታኅሣሥ 22 እስከ ጥር 3, 2016 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል 19 ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ በደብረ ብርሃን እና ፊኖተ ሰላም ከተሞች ከባድ የከተማ ውስጥ ውጊያ ተደርጓል። በተመሳሳይ ጥር 2 ቀን በጎንደር ከተማ በሞርታር የታገዘ ከባድ ውጊያ መደረጉ ተዘግቧል። ውጊያው እንደቀጠለ ቢሆንም የፋኖ የሸምቅ ውጊያ እየተቀዛቀዘ መሆኑን እና መንግሥት የበላይነት እያገኘ እና በትልልቅ እንዲሁም በትናንሽ ከተሞች እንደገና መረጋጋትን እያረጋገጠ ስለመሆኑ ማሳያዎች አሉ። ከእነዚህ ማሳያዎች መካከል የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ዳግም መከፈታቸው፣ በጎንደር እና በባሕርዳር ከተሞች በባጃጅ የሕዝብ ማመላለሻ (ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪ) ላይ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱ እና አጠቃላይ መደበኛ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተጠቃሽ ናቸው።3 ይህ መረጋጋት የመጣው የክልሉ መንግሥት ለፋኖ ታጣቂዎች ትጥቅ በመፍታት ከሕዝብ ጋር ተመልሰው ለመቀላቀል የስልጠና ማዕከል እንዲገቡ አጠቃላይ ጥሪ ካደረገ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው።4
በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር በተያያዘ የተደረገ ውጊያ
የዘይሴ ብሔረሰብ ተወላጆች የሚኖሩበት የዘይሴ ቀበሌ እንደ ልዩ ወረዳ እውቅና እንዲሰጠው እና ልዩ የአስተዳዳር ደረጃ እንዲያገኝ ከሚል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በኤልጎ እና ወዘቃ ቀበሌዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና ማንነቱ በውል ካልታወቀ የታጣቂ ቡድን መካከል በተደረገ ውጊያ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።5 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ታኅሣሥ 23 ቀን ባወጣው መግለጫ በአርባ ምንጭ አካባቢ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ከጋሞ ዞን ስር በመውጣት የራሳቸውን ልዩ ወረዳ ለማቋቋም ካላቸው ፍላጎት ጋር በተያያዘ በአካባቢው “ተደጋጋሚ ግጭቶች” መከሰታቸውን አሳውቋ።6 ከታኅሣሥ 23, 2015 እስከ ታኅሣሥ 21, 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ አክሌድ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር የተያያዙ አራት የፖለቲካ ግጭት ኩነቶችን መዝግቧል። ከእነዚህ ኩነቶች አብዛኛዎቹ በጋሞ ዞን ውስጥ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰቱ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ታኅሣሥ 22 -ጥር 3, 2016*
ይህ መረጃ/ዳታ ከታኅሣሥ 22 እስከ ጥር 3, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
*አክሌድ የሚያወጣውን ዳታ ከኅዳር ወር የመጨረሻዎቹ ቀናት እስከ ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ድረስ በእረፍት ምክንያት አቁሞ ስለነበረ ይህ ዘገባ በተለየ መልኩ ሁለት ሳምንታትን ይሸፍናል።
የኩነት አይነቶች
- ውጊያዎች: 28 ኩነቶች
- ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 1 ኩነት
- ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 7 ኩነቶች
- የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
- ሰልፎች: 2 ኩነቶች
- ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት
Footnotes
- 1
- 2
- 3
አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: ትላልቅ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ በመመለሳቸው ምክንያት አማራ ክልል የእፎይታ ትንፋሽ እየተነፈሰ ነው፣’ ጥር 2, 2016
- 4
አማራ ሚዲያ ኮፖሬሽን፣ “ከ5 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ሰላምን መርጠው ወደ ማዕከሎች ገብተዋል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)፣’ ታኅሣሥ 10, 2016
- 5
- 6
- 7
ይህ ውጊያዎችን፣ ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚመለከቱ ኩነቶችን እንዲሁም የአመፅ ግጭት ንዑስ ኩነት የሆነውን የአመፅ ኩነትን ይጨምራል።
- 8
ይህ የተቃውሞ ሰልፎች የኩነት አይነትን እንዲሁም የአመፅ ግጭት ንዑስ ኩነት የሆነውን ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ ኩነትን ይጨምራል።