Skip to main content

ኢፒኦ ሳምንታዊ ዘገባ (የካቲት 26, 2016)

የአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች.

19 March 2024

Also available in English

የሁኔታዎች አጭር መግለጫ

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል በከተሞች ውስጥ የሚደረጉ ውጊያዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች መካከል መጠነኛ ውጊያ መከሰቱ ተዘግቧል። በሁለቱ ክልሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችም ተዘግበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ እንዲሆን የሚጠይቅ ሰልፍ ተደርጓል። 

በአማራ ክልል የሚደረጉ ውጊያዎች ወደ ከተሞች መስፋፋት

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን ውጊያዎች በባህርዳር፣ ሸዋ ሮቢት፣ ደምበጫ፣ ደብረ ማርቆስ እና መርዓዊ ከተሞች መደረጋቸው ተዘግቧል። ከእነዚህም ውጊያዎች አብዛኛዎቹ የተመዘገቡት በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ ነው። በባህርዳር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻ ያደረጉ ሲሆን በርካታ የፋኖ ታጣቂዎችን ተኩሰው መግደላቸውን እና መያዛቸውን ገልጠዋል።1 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማን መልሶ ለመቆጣጠር ያደረገውን ትልቅ ወታደራዊ ዘመቻ እና በሰሜን ወሎ ዞን የላሊበላ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የተደረገ ውጊያን ጨምሮ በመላው የአማራ ክልል ተጨማሪ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል።2 በተጨማሪም በአዊ፣ ደቡብ ወሎ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። 

በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች 

የካቲት 20 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች መሆናቸው የተገለፀ የታጠቁ ግለሰቦች በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ደጋ ጂጊ አካባቢ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ጥቃት በመፈፀም ሶስት ሰላማዊ ሰዎችን ገድለው ሁለቱን አቁስለዋል። የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ለጥቃቱ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ይኽውም በፋኖ ታጣቂዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ለአጭር ጊዜ የቆየ ውጊያ እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ ክስተት ከመስከረም 2016 በኋላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመ ብሔርን መሠረት ያደረገ የመጀመሪያ ጥቃት ነው። ሁለቱም የአማራ እና የኦሮሞ ብሔሮች ሰሜን ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ላይ የሚኖሩ ሲሆን በሰላማዊ ሰዎች ላይ በታጠቂ ቡድኖች የሚፈፀም ጥቃት በተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው —እና የፋኖ ታጣቂ አማጺዎች ጥቃቱ የከፋ እንዲሆን አድርገውታል። በዚህ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች ላይ በርካታ የግጭት ውስጥ ተሳታፊ አካላትን የሚያካትቱ ሲሆን ከፍተኛ ውጊታውች የተዘገቡት ከሕዳር 22 እስከ ታህሳስ 22, 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። 

በትግራይ ክልል የተደረገ ሰልፍ 

በትግራይ ክልል የካቲት 21 ቀን ጡረተኞች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከጀመረበት ከጥቅምት 2013 ጊዜ ጀምሮ ያልተከፈላቸው የጡረታ ክፍያ እንዲከፈላቸው በመጠየቅ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ በተጨማሪም የፕሪቶሪያ ስምምነት በመንግሥት እና በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር መካከል የተፈረመውየያዛቸው ስምምነቶች እንዲተገበሩ ጠይቀዋል። ጥቅምት 2015 የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሰልፍ ኩነቶችበተደጋጋሚ እየተደረጉ ሲሆን ይኽውም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፋይናንስ፣ የሰዎች መፈናቀል እና ለቀድሞ የትግራይ መከላለያ ኃይል ወታደሮች የህክምና ድጋፍን ለተመለከቱ ጉዳዮች መፍትሄ እንዲሰጥ ጫና ፈጥረውበታል።

ኢትዮጵያ በጨረፍታ
የካቲት 16-22, 2016

ይህ መረጃ/ዳታ ከየካቲት 16-22, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።

  • የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች: 39
  • 33% ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር
  • የሰልፍ ኩነቶች: 1
  • 0% ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር

የኩነት አይነቶች

ውጊያዎች: 32 ኩነቶች

ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 0 ኩነት

ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 7 ኩነቶች

የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት

ሰልፎች: 1 ኩነት

ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት

Share on

Related content